ዘመነ ጽጌ
=====
ዘመነ ጽጌ በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ያሉት ዐርባ ቀናት ዘመነ ጽጌ፤ ወርኃ ጽጌ እንደሚባሉ ይታወቃል።
የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገሥት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል ። “ጾምስ በታወቀው ዕለት፣ በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው።
ይህም ኃጢአቱን ለማስተስረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ህግን ለሰራለት እየታዘዘ፤ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ፤ ሥጋም ለነባቢት ነፍሥ ትታዘዝ ዘንድ ነው።” /ፍት.ነገ.ፍት.መን.አንቀጽ 15፥564/
ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው።
ለፈቃደ ሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው።
ሰው ፈቃደ ሥጋን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት ስንቅ ነው።
“ጾም ቁስለ ነፍስን የምፈውስ፣
ኃይለ ፍትወትንም የምታደክም፣
የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ፣
ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣
የጽሙዳን ክብራቸው፣
የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው፣
የጸሎት ምክንያት/እናት/ የእንባ መገኛ ምንጭ፣
አርምሞን የምታስተምር፣
ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፣
ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት።/ማር ይስ.አንቀጽ 4 ምዕ. 6/
የጾም ዓይነቶች
ጾም በዓይነቱ በሁለት ሊከፈል ይችላል።
የአዋጅና የግል።
የአዋጅ ጾም በይፋ ለሕዝቡ ተነግሮ በአንድነት የሚጾም የትእዛዝና የሕግ ጾም ነው።
በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሁሉም እንዲጾማቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ፣ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ፣ ጽኑ ደዌ፥ሕመም... ካልኖረበት በቀር
ሁሉም ክርስቲያን እንዲጾማቸው የታወጁት ሰባት የዐዋጅ/የሕግ/ አጽዋማት አሉ።
እነዚህም *ሰባቱ አጽዋማት*
1 ጾመ ነቢያት
2 ጾመ ጋድ
3 ጾመ ነነዌ
4 ዐቢይ ጾም
5 ጾመ ሐዋርያት
6 ጾመ ድኅነት(ዓርብ ረቡዕ)
7 ጾመ ፍልሰታ ናቸው ።
ጾም እንዲህ ወራት ተወስኖለት በቁጥር የተወሰነ በጊዜ የተገደበ ይሁን እንጂ የዘለዓለም ሕይወትን ለመውረስ የሚረዳን የጽድቅ መሠረት፣ የገነት በር፣ በአጠቃላይ የክርስቲያኖች ኑሮ ስለ ሆነ።
ከተዘረዘሩት የሕግ አጽዋማት በላይ ከዓመት እስከ ዓመት የሚጾሙ በገዳም፣ በበረሀ ያሉ አንዳንድ መነኩሳትና ባሕታውያን አሉ።
“ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙም ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ ይጠግባሉና እንዳለ።/ማቴ 5፥6፣ኢሳ 41፥55/
አበው ቢቻላችሁስ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ፤ ለድሆችም ምጽዋት ስጡ በማለት እንዳዘዙት ጾምን ቢያዘወትሩ ለስርየተ አበሳ፣ ሥጋን ለመጎሰምና ነፍስን በተግባር ለማሰልጠን ይመቻል።
ይህም ወደ ሁለተኛው የጾም ዓይነት ማለትም ወደ ግል ጾም ይወስደናል።
የግል ጾም እግዚአብሔር ኃይሉንና ብርታቱን የሰጣቸው አንዳንድ ምእመናን በግል/በስውር/ የሚጾሙት ነው።
አንድ ሰው ከእግዚአብሔር የሚፈልገው ነገር ሲኖር፣ ራሱን ለመግዛት ይችል ዘንድ እንዲሁም ንስሐ ገብቶ የንስሐ አባቱ ሲያዝለት በግሉ ይጾማል።
ይህም ከጥንት ጀምሮ የነበረ ሥርዓት ነው።
ለአብነት ያህል ሊቀ ነቢያት ሙሴን፣ ነቢዩ ዳንኤልን፣ ነቢዩ ዳዊትን፣ ነህምያን፣
በሐዲስ ኪዳን ቅ.ጳውሎስንና ቅ.ጴጥሮስ መጥቀስ ይቻላል።
የግል ጾም የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል።
የንስሐ ጾም ኃጢአት የሠሩ ምእመናን ከመምህረ ንስሐቸው ጋር ተመካክረው ንስሐ ገብተው በአንቀጸ ንስሐ መሠረት ቀኖና ሲሰጣቸው የሚጾሙት ጾም ነው።
ቀኖናውን የሚፈጽሙት ማንም ሰው ሳያውቅባቸው በስውር ይሆናል።
የፈቃድ ጾም በሌላ አጠራር የትሩፋት ጾም በመባል ይታወቃል።
በዝግ ወይም በማኅበር ሊፈጸም ይችላል።
እግዚአብሔርን በትጋት የሚያገለግሉ ምእመናን በግል ወይም በማኅበር በገዳም የሚኖሩ አባቶች በአንድነት ስለሚከተሉት ምክንያቶችና ስለ መሰሎቻቸውም የፈቃድ ጾምን ይጾማሉ።
1) በግልና በቤተሰባዊ ሕይወታቸው የገጠማቸው ችግር ካለ እንዲወገድላቸው በሚኖሩባት አገርና በቤተ ክርስቲያናቸው ዙሪያ ያላቸው እክል እንዲርቅላቸው፤
2) ክቡር ዳዊት “ነፍሴን በጾም አስመረርኳት እንዳለ ራሳቸውን መግዛት ይችሉ ዘንድ፥ ነፍስን በሥጋ ላይ ለማሰልጠን፤
3) በጥቂት ሲለምኑት አብዝቶ የሚሰጥ እግዚአብሔር ምሥጢር እንዲገልጥላቸው ፤
4) መንፈሳዊ ተግባራትን ለመፈጸም ከፈጣሪያቸው ፈቃድና እርዳታ ለመጠየቅ፤
5) የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ የቅዱሳንን መከራ እያሰቡ በረከታቸውን ለመሳተፍ ከኃጢአት ለመንጻት የሚሉት ናቸው።
አንዳንድ መነኮሳት፣ ባህታውያንና ምእመናን በፈቃድ የሚጾሟቸው የታወቁ ጊዚያት አሉ።
እነዚህም ወርኃ ጽጌና ወርኃ ጳጉሜን “ጾመ ዮዲት” ናቸው።
ዘመነ ጽጌ፦ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ያለው አንድ ወር ከዐሥር ቀን ወይም 40 ቀን ወርኃ ጽጌ፣ ዘመነ ጽጌ፣ ተብሎ ይጠራል።
በእነዚህም ቀናት በየቤተ ክርስቲያኑ የሚነበቡ ምንባቦች፣ የሚዘመሩ መዝሙሮች፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚቆመው ማኅሌት፣ በጠቅላላው የሚነገረው ስብሐተ እግዚአብሔር ሁሉ ሰማይ በከዋከብት ምድር በጽጌያት አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው።
በወርኃ ጽጌ ለሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት መነሻው “መልአኩ ሕፃኑና እናቱን ወደ ግብጽ ይዘሃቸው ሽሽ፤ የሕፃኑን ነፍስ ሊገድሉት ይሻሉና” ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሠረት ዮሴፍም ሕፃኑንና እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ ወደ ግብፅ መሰደዱና እመቤታችንና ሕፃኑ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ/ራእ 12፥16/ ወደ አገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው።
ይህንንም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሱ አባ ጽጌ ብርሃን “የሮማን ሽቱ የቀናንሞስ አበባ የምትሆኝ ማርያም ሆይ፥ በረኃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪ ጠወልግ ድረስ በስደትና በለቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እኅትሽ እንደ ሰሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፤ በዚህም ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር ።
”እንዲሁም አባ አርከ ሥሉስ በስደቷ የደረሰባትን ኀዘን፣ ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት “ሰቆቃወ ድንግል”በሚለው ድርሰታቸው እንዲህ አሉ፦
“ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሽ ጊዜ የደረሱብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንዳጎበጎቡ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር።”
የማኅሌተ ጽጌና የወርኃ ጽጌ አጀማመር
የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው።
በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጥዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅ.ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌተ ጽጌና ከሰቆቃወ ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው።
ዝክሩም በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፥ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢው ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም ያሚዘክሩት ነው።
አቅመ ደካሞች ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል።
*ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው።*
የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ዜና ገድል የጽጌን ጾም አስመልክቶ የሚከተለውን ይተርካል፦“አባ ጽጌ ብርሃን የተባለው አባት እንደ መዝሙረ ዳዊት መቶ ሐምሳ አድርጎ ማኅሌተ ጽጌን ደረሰ።
አባ ጽጌ ብርሃን ይህንን በደረሰበት ጊዜ የወረኢሉ ተወላጅና የደብረ ሐንታው አባ ገብረ ማርያም አማካሪው ነበር።
ድርሰቱንም ሲደርስ ቤት እየመታና በአምስት ስንኝ እየከፋፈለ ነው።
አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም ከመስከረም 26 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ማኅሌተ ጽጌን ለመቆምና የጽጌን ጾም ለመጾም በየዓመቱ በደብረ ብሥራት እየመጡ ይሰነብቱና ቁስቋምን ውለው ወደየበአታቸው ይመለሱ ነበር።”
ከአባታችን የገድል ክፍል ለመረዳት እንደሚቻለው አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም የጽጌን ማኅሌት መቆም ወቅቱንም በፈቃዳቸው መጾም ጀምረዋል።
ዘመኑም በ14ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።
ከዚያ ወዲህ ግን ጥቂት በጥቂት እያለ አብያተ ክርስቲያናት በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ጀመሩ።
*ጥቂት መነኩሳትና አንዳንድ ምእመናን በፈቃዳቸው ወቅቱን መጾም ጀመሩ።*
በዘመናችን በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ስለ ተለመደ ከማታው በሦስት ሰዓት ይደወላል።
ሴት ወንዱ፥ ትንሹም ትልቁም ይሰባሰባል፤ ማኅሌተ ጽጌው እየተዜመ፤ አስፈላጊ የሆነው በጽናጽል በከበሮ እየተወረበና እየተሸበሸበ እስከ ጥዋቱ 12 ሰዓት ድረስ ተቁሞ ይታደራል።
*የጽጌ ጾም የውዴታ/የፈቃድ/እንጂ የግዴታ አይደለም።*
*የእመቤታችን ስደት በማሰብ ከትሩፋት ወገን የሚጾም ስለ ሆነ ምእመናን ሁሉ እንዲጾሙት አይገደዱም፤ የሚጾመው የማይጾመውን ለምን አልጾምክም ብሎ ሊፈርድበት ስለ ራሱም እየጾምኩ ነው ብሎ መናገር አይገባውም።*
የፈቃድ መሆኑንም የሚያሳየው ይኸው ነው።
የማይጾመውም በልቡ ያመሰግናል፤ ስደቷን እያሰበ ማኅሌቷን እየዘመረ ያሳልፋል።
ሁለተኛው የፈቃድ ጾም ጾመ ዮዲት ሲሆን በሀገራችን ምእመናን ጾመ ጳጉሜን በማለት ይጠሩታል።
እንደ ጽጌ የፈቃድ ጾም የታወቀ ባይሆንም በዓመቱ መጨረሻ ወር በጳጉሜን የሚጾም ነው።
የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው። ዮዲ 2፥2-7
ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው።
ስለዚህ ምእመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንና ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው በጳጉሜን ወር ይጾማሉ።
ኃጢአታቸውን ለንስሐ አባታቸው ተናግረው ተናዘው ቀኖና ተቀብለው የሚጾሙም አሉ።
በሌላ በኩል የጳጉሜን ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብባት ስለ ሆነች ያን እያሰቡ የሚጾሙ አያሌ ናቸው።
ጳጉሜን የዓመታት መሸጋገሪያ እንደ ሆነች ምጽአትም ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው ዓለም መሸጋገሪያ ነውና።